Δευτέρα 15 Ιουνίου 2020

መሠረታዊ ኦርቶዶክስ አስተምህሮ - ኦርቶዶክሳዊ ነገረ ሰብእ

ዝግጅት በ: ሮ. ኢ.፣ . ገ.
 
**በዚህ ጽሑፍ ላይ የተጠቀሱት የቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስና የእኅቱ የቅድስት ማቅሪና በግሪክ የተጻፉ ትምህርቶች ከተለመዱት የግሪክ ጽሑፎች በጥቂቱ ውስብስብ ስለሆኑ ወደ አማርኛ መተርጎሙን በተወሰነ ፈታኝ አድርገውታል። በትርጉሙ ሥራ ላይ የተቻለንን ያደረግን ሲሆን ለማጣቀሻ ይሆን ዘንድ ዋናውን ግሪክና የእንግሊዝኛ ትርጉማችንን አያይዘናል።

ከኦርቶዶክሳዊ ትውፊት እንደምንረዳው ኦርቶዶክሳዊ ነገረ መለኮት ቅዱሳት መጻሕፍትን በቀጥታ ንባብ ወይም በትርጓሜ ብቻ ከመረዳት ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ እገዛ እንደ እግዚአብሔር ሕግ ከመኖር የሕይወት ልምምድ[1]፣ ሰው ተኮር ከሆነ የአብርሆት ሂደት እና ከሱታፌ አምላክ (‘θέωσις’; theosis)[2] የመነጨ ነው፡፡ የእውነት መንፈስ የመራቸው የቤተክርስቲያን ቅዱሳን አባቶች ትምህርት እና ሕይወትም እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ ቅቡል የሆኑበት ይሄ የሕይወት ልምምድ አብዛኛውን የቤተክርስቲያኗን ትውፊት ቅርጽ ያስያዘ ነው፡፡ ይሄም አማኞችን ስለ ኦርቶዶክሳዊ ንቃተ ሕሊና (φρόνημα’; phronema)[3] ያም ማለት ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳን የሕይወት ልምምድ ላይ ስለተመሠረተ ኦርቶዶክሳዊ አስተሳሰብ እንዲናገሩ ያስችላቸዋል፡፡ ቅዱሳን ምንም ስንኳ በተለያዩ ዘመናት ላይ የነበሩ ቢሆኑም የነገረ መለኮት ግንዛቤ በጸሎት እና ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖር ኅብረት ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ሁሉም ተመሳሳይ የሆነ ነገረ መለኮታዊ ግንዛቤ ነበራቸው፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን በስብእናቸውም ሆነ በአኗኗር ሁኔታቸው ቢለያዩም ተመሳሳይ የሆነ ኦርቶዶክሳዊ ንቃተ ሕሊና ነበራቸው፡፡ ይሄን ስንል ግን ቅዱሳን ሰዎች ፈጽመው አይሳሳቱም ማለታችን አይደለም፤ ሰው እንደመሆናቸውም ሰዋዊ ጠባያቸው ተጽእኖ ሊያደርግባቸው የሚችልበት ዕድል ይኖራል፡፡ 
አንዳንድ ሃይማኖታዊ ርእሰ ጉዳዮች በአባቶች እና እናቶች በጥልቀትና በብዛት የተዳሰሱ ቢሆንም ብዙም ያልተነገረባቸው ርእሰ ጉዳዮችም አሉ፤ ነፍስ ወደ መኖር እንዴት ነው የምትመጣው የሚለውንና ባሕርየ ልቡና እንዴት ያለ ነው[4] የሚለውን እንደምሳሌ መውሰድ ይቻላል፡፡ ይሄ የሚሆነው አምላካዊ አሠራር (ኦይኮኖሚኣ)[5] ምክንያት ሊሆን ይችላል ያም ማለት አንዳንድ ጉዳዮች መለኮታዊ ምሥጢርን በአግባቡ መግለጽ በማይችለው በሰው ቋንቋ ቢገለጡ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ሊያመዝን ስለሚችል ማለት ነው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ቅዱሳኑ የነገረ መለኮት ሊቃውንት አንዳንድ ርእሶችን ሳያነሡአቸው የቀሩት በወቅቱ ከነበረው ማኅበረሰብ አንጻር አስፈላጊ ስላልመሰላቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ አንዳንድ ቅዱሳን ብቻ ሌሎች ቅዱሳን ዝምታን የመረጡባቸውን አንዳንድ ርእሰ ጉዳዮች እጅግ በጥልቀት በመመልከታቸው ምክንያት  ሊሆን ይችላል፡፡ በአንጻሩ እንደ የሥጋና ነፍስ አብሮ መኖር እና ይሄ ከሱታፌ አምላክ ጋር ያለውን ቁርኝትን የሚያወሱ እና ሌሎች አያሌ ጉዳዮች ደግሞ በብዛትና በግልጽ የተዳሰሱ ናቸው፡፡ ከዚህ በመቀጠል ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ከሐዋርያት ትምህርትና ከአባቶች ትርጓሜ በመነሣት ስለ ሥነ ሰብእ የምታስተምረውን ትምህርት እናቀርባለን፡፡ 
        
የኦርቶዶክሳዊ ሥነ ሰብእ ማብራርያ
ኦርቶዶክሳዊው ትውፊት እግዚአብሔር ሰውን (ወንድና ሴት) በመልኩና በአምሳሉ እንደፈጠረው ያስተምራል፡፡[6] ‹መልክ› ለሁሉ የተሰጠ መለኮታዊ ስጦታ ሲሆን ‹አምሳል› ግን ነጻ ፍጥረት የሆነውን የሰውን ልጅ ሱታፌ የሚፈልግ ነው፡፡ የመጀመርያዎቹ ጥንዶች የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመተላለፋቸውና ሰው በመውደቁ ምክንያት የሰው ልጅ እግዚአብሔርን የመምሰል ሂደት እንዳይፈጸምለት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በውድቀቱ ምክንያትም ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ኅብረት ተቋረጠ የሰውም እውቀት የተዳፈነ ሆነ፡፡ ከዛ ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጅ ለሞት ብቻ ሳይሆን ለሥጋ ፍትወታት ሁሉ የተገዛ ሆነ
የኒሳው ጳጳስ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ‹ስለ ሰው አፈጣጠር› (ΠΕΡΙ ΚΑΤΑΣΚΕΥΗΣ ΑΝΘΡΩΠΟΥ) ባስተማረው ትምህርቱ የሰው በእግዚአብሔር መልክ መፈጠር ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚመሳሰልባቸው (በጸጋ ከእግዚአብሔር ያገኛቸው) ባሕርያት እንዲኖሩት መሆን ማለት ሲሆን እግዚአብሔርን የመምስል ሂደት ሳይፈጸምለት መቅረት ደግሞ በሌላ በኩል ሰው ከእግዚአብሔር መራቁንና መለየቱን የሚናገር ነው ይላል፡፡[7] እንደ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ከሆነ ከሰው ውስጥ ለመለኮታዊ ባሕርይ ቅርብ የሆነችው የማትሞተውና የማትጠፋው ሰው ሁሉ በተፈጥሮ ገንዘብ የሚያደርጋት ለባዊት የሆነችው ነፍስ ናት፡፡ ምንም ስንኳ ነፍሳችን ካልተፈጠረውና ውላጤ ከማይስማማው ከመለኮት ባሕርይ በተቃራኒ የተፈጠረችና ውላጤ የሚስማማት ብትሆንም ኢ-ቁሳዊነትን፣ ኢ-መዋቲነትን እና ለባዊነትን በጸጋ ገንዘብ አድርጋለች፡፡ ይህም ነፍስን ለባዊ ካልሆነው ይልቅስ ሟችና ጠፊ ከሆነው ከግዙፉ ሥጋ የበላይ ያደርጋታል፡፡ ነገር ግን ይህች ማእከሏን ልብን ያደረገች ረቂቅ የሆነች ነፍሳችን ያለ ሥጋ ነገሮችን ለመረዳት (በስሜት ሕዋሳት) እና ምላሽ ለመስጠት (በእንቅስቃሴ ወይም በድርጊት) አይቻላትም፡፡ የሥጋ አካላት በደንብ ካልጠነከሩ ወይም ጉዳት ከደረሰባቸው የነፍስ ግብረ ባሕርይዋ የሆኑ ነገሮች ሁሉ በምልአት መገለጥ አይችሉም፡፡ ይህ በልቡና እና በአካል መካከል ያለ ተዋሕዶ[8] እንደ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ከሆነ በቃላት የማይገለጽ ነው፡
ነገር ግን በልቡና[9] እና በአካል መካከል ያለው ተዋሕዶ ልንናገረውና ልንረዳው የማንችለው ነው ፤ በውስጡ በመሆን ያይደለ (ግዙፍ ያልሆነ ነገር ግዙፍ በሆነ ነገር አይያዝምና) ከውጪ ሆኖ በመክበብም ያይደለ (ግዙፍ ያልሆነ ነገር ማቀፍ [መጠቅለል] አይችልምና) ነገር ግን ለመረዳትና ለመግለጽ በማይቻል መንገድ ልቡናችን ባሕርይአችንን ስለሚዋሐድ በመተከል (ጠብቆ ይነበብ) ወይም በመጠቅለል ሳይሆን ልናስበውና ልንናገረው በማንችለው መንገድ ከውስጥም አለ ደግሞም በውጭ ይከባል ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ተፈጥሮ በራሷ መንገድ ስትጓዝ ልቡናም እንዲሁ እንደሚያደርግ፤ ነገር ግን ተፈጥሮ በአጋጣሚ ከአነዋወሯ ብትናጠብ የአእምሮ እንቅስቃሴም እንዲሁ እንደሚደናቀፍ ከማወቃችን በቀር እንዴት እንደሚሆን አናውቅም፡፡[10]   
ነፍስና ሥጋ የተዋሐዱ ብቻ ሳይሆኑ ያለመቀዳደም በአንድ ጊዜ የሚገኙ ጭምር ናቸው፡፡ ይሄ ዐሳብ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ለዕረፍተ ሥጋ ከተቃረበችው እኅቱ ከቅድስት ማቅሪና ጋር ባደረገውና እርሷ በፍልስፍናው ዓለም በዘመኑ ነፍስ ከሥጋ ጋር ያለውን ግኙነት በተመለከተ እውነት ተብለው የሚወሰዱ አያሌ እሳቤዎችን ሐሰተኝነት በቀላሉ ባጋለጠችበት ውይይት ላይ ግልጽ በሆነ ሁኔታ አጽንኦት ተሰጥቶታል፡፡ ቅድስት ማቅሪና ርቱዕ በሆነ አንደበት ይህንን ስታብራራ፡
እንደገናም በሌላ በኩል ማገናዘብ የሚችል ማንኛውም ሰው ነፍስ ከሥጋ ዘግይታ ተገኝታለች ያም ማለት የሥጋ ቅርጽ መያዝ ይቀድማታል ብሎ አያስብም ምክንያቱም ሁሉም ሰው በራሱ ማየት እንደሚችለው ግዑዝ የሆነ ወይም ነፍስ የሌለው ነገር ሊንቀሳቀስ ወይም አካላዊ ዕድገት ሊኖረው አይችልም፤ በማኅጸን ያለ ፅንስ ደግሞ እንደሚያድግም በማኅጸን ውስጥም እንደሚንቀሳቀስም ጥርጥር የለውም፡፡ ከዚህ በመነሣት የነፍስና የሥጋ የህልውናቸው መጀመሪያ ተመሳሳይ ቅጽበት መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል፡፡ ልክ መሬት ከገበሬ ችግኝን ተቀብሎ ለችግኙ ዕድገት የሚያስፈልገውን ሁኔታ አመቻችቶ ዛፍ እንደሚያበቅል፤ ነገር ግን ችግኙ የማደግ ኃይልን ከመሬቱ ሳይሆን ከተፈጥሮ እንዲያገኘው ሁሉ በተመሳሳይ ሁኔታ ያ ሰውን ለማስገኝት በሰው ውስጥ የሚተከለውም ሕይወት ካለው በመገኘቱ ሕይወት ያለው ሲሆን በተመቻቸለት ሁኔታ በተፈጥሮ ባገኘው ኃይል በራሱ የሚያድግ ነው፡፡[11] ትላለች፡፡
ይህ ምላሽ እንደሚያረጋግጠው ስለ ነፍስና ሥጋ ሊኖረን የሚገባው መረዳት ሁለቱም እኩል በተመሳሳይ ቅጽበት እንደሚገኙ ነው፡፡ በተጨማሪም በሕይወት ያለ የሰው አካል የማደግ ተፈጥሮአዊ ጸጋ ተሰጥቶታል ይሄም ነፍስ ባሕሪዋን ሙሉ በሙሉ ትገልጽ ዘንድ አስፈላጊ ነው፡፡ በተያያዥም የልዮኑ ጳጳስ ቅዱስ ሄሬኔዎስ ምንም ስንኳ ሥጋ ራሱ ዝግ ብሎ ነፍስንም የሚያዘገያት ቢሆንም ለግብረ ባሕርይዋ መሣርያ የሚሆናት ግን እርሱ ነው ይላል፡፡[12]
ኦርቶዶክሳዊ ነገረ መለኮት በእግዚአብሔር መልክና አምሳል መፈጠር ለእያንዳንዱ ሰብአዊ ፍጥረት በእግዚአብሔር ጸጋና ከመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋይ (ሱታፌ አምላክ) በመሆን ከወደቀው ሰዋዊ ባሕርይ ሊሻገር የሚችልበትን ችሎታ እንደሚያጎናጽፈው ይረዳል፡፡ ይህ ጸጋ የሚገኘውም ራሷ ክርስቶስ በሆነላት በቤተክርስቲያን አካል ኅብረት ማድረግ በሚገኝባቸው ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን በመካፈል እና ራስን በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ በነፍስም በሥጋም በኦርቶዶክሳዊ ሥነ ምግባራት በማነጽ ነው፡፡ አንድ ሰው በዚህ መንገድ (ሂደት) ውስት ሲያልፍ በነፍሱ ያለ (በተፈጥሮ በጸጋ የተገኘ) መለኮታዊ ባሕርይ ይጠነክራል፣ ሥጋውም ከፍትወታት ይነጻል፡፡ በተጨማሪም ልቡና ከእግዚአብሔር ጋር በሚያደርገው ኅብረት አብርሆትን ገንዘብ እያደረገ ሲመጣ አእምሮውም (‘διάνοια; dianoia) ብሩህ ይሆናል ይሄም ተፈጥሮአዊ ከሆነው የመረዳት ዐቅም በመሻገር መለኮታዊ የሆነውን ጥበብ መረዳት የሚችልበትን ጸጋ ያጎናጽፈዋል፡፡          


[1] ዮሐ 14፡15-21
[2] ይህም በአንጽሆተ ልብ፣ በአብርሆተ ልቡና እና ከመለኮት ባሕርይ ተካፋይ በመሆን ደረጃዎች ወደ ቅድስና ሕይወት የሚደረግ ጉዞን ያመለክታል፡፡ ነገረ ልቡናዊ ነገረ መለኮትም ከዚሁ የሚመነጭ ነው፡፡
[3] ፍሮኒማ የሚለው ቃል ‹ንቃተ ሕሊና› የሚል ትርጉምን ሊይዝ ይችላል፡፡ የግሪኩ ቃል እንደሚገልጸው ከሆነ ፍሮኒማ ኦርቶዶክሳዊ እምነትን በተግባር ከመኖር የሚመነጭ እይታ ነው፡፡
[4] ΠΕΡΙ ΚΑΤΑΣΚΕΥΗΣ ΑΝΘΡΩΠΟΥ, Γρηγορίου Νύσσης, Άπαντα τόμος 5, σειρά: “Έλληνες Πατέρες της Εκκλησίας” αρ. 91 (Θεσσαλονίκη, 1987), σελ. 70.
[5] አንዳንድ ነገሮች ከኦርቶዶክሳዊ እሳቤዋች አንጻር ልክ ባይመስሉም የማይታይ መንፈሳዊ ጥቅም እንድናገኝባቸውና በዋናነትም ለድኅነታችን ሲባል ለጊዜው ሊፈቀዱ ይችላሉ፡፡ ይሄም አምላካዊ አሠራር (ኦይኮኖሚያ) በመባል ይታወቃል፡፡
[7] ΠΕΡΙ ΚΑΤΑΣΚΕΥΗΣ ΑΝΘΡΩΠΟΥ, Γρηγορίου Νύσσης, Άπαντα τόμος 5, σειρά: “Έλληνες Πατέρες της
Εκκλησίας” αρ. 91 (Θεσσαλονίκη, 1987), σελ. 113-127.
[8] ቅዱስ ጎርጎርዮስ የተጠቀመው ቃል ኪኖኒያ (‘κοινωνία’) ሲሆን ያም የሥጋና የነፍስ ተዋሕዶን የሚገልጽ ቃል ነው። ተዋሕዶ ኤኖሲስም ኪኖኒያም የሚሉትን ቃላት የሚተረጉም ሲሆን እዚህ የተጠቀምነው የሥጋና የነፍስ ተዋሕዶን ለመግለጽ የገባ ነው።
[9] ልቡና የነፍስ ግብረ ባሕርይዋ፣ የነፍስ ዓይኗ ነው፡፡
[10] « Ή  δε  τού νου  πρoς τo  σωματικόν  κοινωνία  άφραστόν τε  και  άνεπινόητον  την  συνάφειαν  έχει,  ούτε  έντoς  ουσα  (ούτε γάρ  έγκρατεΐται  σώματι  τδο  άσώματον),  ούτε έκτος περιέχουσα (ού γάρ περιλαμβάνει  τι  τά  άσώματα) άλλα  κατά  τινα  τρόπον άμήχανόν  τε  και  άκατανόητον  έγγίζων  ό  νους  τη  φύσει  και προσαπτόμενος,  και  έν  αύτή  και  περί  αύτήν  θεωρείται,  ούτε έγκαθήμενος  ούτε  περιπτυσσόμενος.  ’Αλλά  πώς,  ούκ  έστιν  είπεΐν  ή νοήσαι,  πλήν οτι  κατά τδν ίδιον αύτής είρμον εύοδουμέ-νης τής φύσεως, και ό νους ένεργος γίνεται' εί δέ τι πλημμέλημαπερί ταύτην συμπέσοι,  σκάζει κατ’ έκεϊνο και τής διανοίας ή κίνησις.» ΠΕΡΙ ΚΑΤΑΣΚΕΥΗΣ ΑΝΘΡΩΠΟΥ, Γρηγορίου Νύσσης, Άπαντα τόμος 5, σειρά: “Έλληνες Πατέρες της Εκκλησίας” αρ. 91 (Θεσσαλονίκη, 1987), σελ. 110. በእንግሊዝኛ አንድ ተርጉም: “However, the communion of the nous with the bodily has an ineffable and inconceivable coherence by neither being within it (because the incorporeal cannot be held within a body), nor by containing it externally (because the incorporeal cannot contain anything), but the nous, when approaching and attaching to it (the bodily) by nature in a certain undevised and incomprehensible way, is regarded as both within it and around it –neither seated within it nor wrapped around it. But how (this is so), cannot be expressed or comprehended, except that when nature advances according to its own rhythm, the nous is also activated; and if a certain fault coincides with it,  then the movement of the intellect falters respectively.”
[11] «Ἀλλὰ μὴν ἐφυστερίζειν τὰς ψυχὰς τὴν γένεσιν, καὶ νεωτέρας τῆς τῶν σωμάτων εἶναι συμπλάσεως, οὐδεὶς ἂν τῶν εὖ φρονούντων ὑπονοήσειεν, φανεροῦ πᾶσιν ὄντος ὅτι οὐδὲν τῶν ἀψύχων κινητικήν τε καὶ αὐξητικὴν ἐν ἑαυτῷ δύναμιν ἔχει. Τῶν δ᾿ ἐν νηδύϊ ἐντρεφομένων, οὔτε ἡ αὔξησις, οὔτε ἡ τοπικὴ κίνησίς ἐστινἀμφίβολος. Λείπεται οὖν μίαν καὶ τὴν αὐτὴν ψυχῆς τε καὶ σώματος ἀρχὴν τῆς  συστάσεως οἴεσθαι. Καὶ ὥσπερ τῆς ῥίζης τὴν ἀποσπάδα λαβοῦσα παρὰ τῶν γεηπόνων ἡ γῆ δένδρον ἐποίησεν, οὐκ αὐτὴ τὴν αὐξητικὴν ἐνθεῖσα τῷ τρεφομένῳ δύναμιν, ἀλλὰ μόνον τὰς πρὸς τὴν αὔξησιν  ἀφορμὰς ἐνιεῖσα τῷ ἐκκειμένῳ, οὕτω φαμὲν, καὶ τὸ ἐκ τοῦ ἀνθρώπου ἀποσπώμενον πρὸς ἀνθρώπου φυτείαν, καὶ αὐτὸ τρόπον τινὰ ζῶον εἶναι ἐξ ἐμψύχου ἔμψυχον, ἐκ τρεφομένου τρεφόμενον.» ΠΕΡΙ ΨΥΧΗΣ ΚΑΙ ΑΝΑΣΤΑΣΕΩΣ Ο ΛΟΓΟΣ Ο ΛΕΓΟΜΕΝΟΣ ΤΑ  ΜΑΚΡΙΝΙΑ, Γρηγορίου Νύσσης, Άπαντα τόμος 5, σειρά: “Έλληνες Πατέρες της Εκκλησίας” αρ. 91 (Θεσσαλονίκη, 1987), σελ. 342-344. በእንግሊዝኛ አንድ ትርጉም: “But no-one who is right-minded would suggest/propose a subsequent genesis of souls and consider that it is more recent than the co-fashioning of bodies, given that it is obvious to everyone that none of the soul-less things has kinetic and incremental power within itself. As for those nurtured within the womb, neither the increment nor the local movement is doubted. It remains therefore that we must think that the point of commencement of existence is one and the same for body and soul. And just as the earth receives from the agriculturist an offshoot from the root and creates a tree but does not insert that incremental power within the offshoot being nurtured, except only the causes for increment residing within that segment, thus we say that likewise what is extracted from a human for planting a human, it too is human/animate, and is a living thing from a living thing, nurtured by that which was nurtured.”
[12]  Αγίου Ειρηναίου (Β Αιώνας), Έλεγχος και ανατροπή τής ψευδωνύμου γνώσεως, Βιβλίο 2ο, λγ: 4 - λδ: 1. 

Δεν υπάρχουν σχόλια:

Δημοσίευση σχολίου